የኮሚሽነር ጄኔራል መልዕክት

ኢትዮጵያ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የፖሊስ ተቋም ባለቤት ስትሆን ፖሊስ በዘመናዊ ቁመና ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ 116ኛው ዓመት በዓል ላይ ሆነን አሁን ላይ የደረሰበትን ከፍታ ለሀገራችን ሕዝብና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀንን በታላቅ ድምቀት እያከበርን እንገኛለን።
ፖሊስ በዳግማዊ ምኒልክ ሚያዝያ 29 ቀን 1901 ዓ.ም ለሊት ሌባ እንዳይበዛ፣ ቀን አነባብሮ እንዳያነሳ፤ ክፉን ነገር ሁሉ የሚጠብቅ መለያ ልብስ ያለው ዘመናዊ የፖሊስ ድርጅት በአዋጅ ተቋቁሞ ሲሰራበት ከቆየ በኋላ በአፄ ኃይለ ስላሴ ጥር 23 ቀን 1934 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የፖሊስ ሠራዊት በሚል ስያሜ በአዋጅ ተቋቁሞ ለረዥም ዘመናት በተለያዩ መጠሪያዎች እና አደረጃጀቶች እየተመራ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ሕዝቡን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
ይህ ረዥም ዕድሜና ደማቅ ታሪክ ያለው የፖሊስ ተቋም በሂደት ከነበሩ ሥርዓቶችና የፖለቲካ ሂደቶች ጋር በመቆራኘቱ የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ የፖሊሳዊ ሙያ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት የነበረበት፣ የፖሊስ ክብርና ባህል ተዳክሞ፣ ከስልጣኔ ማማ ወርዶ፣ ከሙያዊ መርህ አፈንግጦ፣ በሕዝብ ዘንድ ሊኖረው የሚገባውን ተቀባይነት አጥቶ በዕድሜው ልክ ሀገራችን በምትፈልግበት የዕድገት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ቆይቷል፡፡
ከሪፎርሙ በፊት በሀገራችን ሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በስፋት በመፈፀማቸው፣ የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባለመቻሉ እንዲሁም ሕዝብ ሲያነሳቸው ለነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየደረጃው ያለው አመራር ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ተቃውሟቸውን እያሰሙ መስዋዕትነትም በመክፈል ጭምር ታግለው በሀገራችን ለውጥ እንዲመጣ አድርገዋል፡፡
የለውጡ መንግስት ፖሊስን ጨምሮ የደህንነትና የሕግ አስከባሪ ተቋማትን የማሻሻል፣ የማጠናከርና ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ የሙያ ተቋም እንዲፈጠር ለማድረግ፣ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት፣ በፖሊስ ተቋም ውስጥ ለዘመናት የተወዘፉ ችግሮችን በመፍታት ከሚመጣውና ከሚሄደው መንግሥት ስርዓት ጋር አብሮ አየፈረሰ ከዜሮ እንዳይጀምር ተቋሙ አቅሙን እያሳደገ ከፓለቲካ ወገንተኝነት የፀዳና ሙያዊ አቅም ላይ የተመሠረተ የፖሊስ ተቋም እየተገነባ ይገኛል፡፡
ከሪፎርሙ በፊት በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ምርመራ በነበረው የብቃት ማነስ፣ በዲስፒሊን ግድፈት እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ይወቀስ የነበረው ፖሊስ አሁን ላይ በቴክኖሎጂ ታግዞ በግልጸኝነትና በተጠያቂነት ውጤታማ የወንጀል መከላከል እና የምርመራ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሀገር አቀፍ የፖሊስ ተቋምን የመለወጥ መርህን ተከትሎ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል መረጃ መርና ማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል መርህን (Intelligence Led and Community Policing Crime Prevention model) በመከተል ሪፎርሙን ተግባራዊ እያደረገ ነው።
ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ውጤታማ የምርመራ ሥራ ለማከናወን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማስረጃ እና መረጃ መር የወንጀል ምርመራ (Evidence and Intelligence Led based Crime Investigation model) መርህን በመከተል ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ የሚመራበትን የፖሊስ ዶክትሪን በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በማዘጋጀት ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ውዝፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥናት በማካሄድ መዋቅራዊ አደረጃጀት በማስተካከል፣ የተለያዩ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ በሎጀስቲክስ ለወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን፣ ትጥቆችንና ዘመናዊ መሣሪያዎችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት እንዲሁም የሰው ኃይል የማስፈፀም እና የመፈፀም አቅም በማጎልበት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ትርጉም ባለው ደረጃ በማሻሻል በሚሰጠው አገልግሎት የሕዝብ አመኔታ ማሳደግ ተችሏል።
የፖሊስ ሥራን በቴክኖሎጂ ለማገዝ በተደረገው ጥረት ተቋሙን ከአምስቱ ምርጥ የአፍሪካ ፖሊስ ተቋማት መካከል የሚያሰልፉትን ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ሲሆን የCCTV ካሜራ አቅም፣ 991 ጥቆማ መስጫ ነፃ የስልክ መስመር፣ ሕዝቡ ወንጀል ለመከላከል እና መረጃ ለመስጠት የሚያችለውን የዜጎች መተግበሪያ (EFPApp) ጋር በማስተሳሰር የተሟላ መረጃ ከየትኛውም የሀገራችን አካባቢዎች በድሮን የሚሠሩ ቅኝቶችና ኦፕሬሽኖችን ለኮማንድ ኮንትሮል ማዕከል በቀጥታ (live) በማስተላለፍ የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ሥራን እንዲሁም የኢንተለጀንስ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ አዲስና ትልቅ አቅም የፈጠረ ቴክኖሎጂ ማልማት ተችሏል።እንዲሁም ዘመናዊና ዲጂታል የሬድዮ ግንኙነት ስርዓት በመፍጠር የተቀናጁ ኦፕሬሽኖችን መምራት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል፡፡
ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊሰ አገልግሎትን ለማዘመን የዲጂታል ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ተሳትፎን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) በማበልፀግ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ህብረተሰቡም መተግበሪያውን በመጠቀም መረጃዎችን ወደ ማዕከሉ በመላክ በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ምርመራ ያለውን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ተችሏል።
በወንጀል ምርመራ ረገድም በሀገራችን እና በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል በማስገንባት ጭምር የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ የDNA ምርመራ ላበራቶሪ ተደራጅቶ ወደ ስራ እንዲገባ በመደረጉ ለፍትህ ሥርዓቱ መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም ባሻገር የተገልጋዮችን እንግልት በማስቀረት ሀገራችን ለምርመራ ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል፡፡እንዲሁም የልህቀት ማዕከሉ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡በምርመራ ስራችን ከዚህ በፊት ይታወቅበት የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማስቀረት ዛሬ ላይ ዓለም ዓቀፍ ፣አህጉራዊና ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጭምር እውቅና እየሰጡት የሚገኝ ተቋም ሆኗል፡፡
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ከሚገኙ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን ግንኙነት በማሳደግ በተሰሩ ጠንካራ ሥራዎች በውጭ ሀገር የትምህርትና የሥልጠና ዕድል፣ የሎጂስቲክ ድጋፍ እና የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር በማድረግ የሠራዊቱ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል።
የሠራዊቱ የመፈፀም ብቃት በማደጉም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ሁነቶች ያለምንም የፀጥታ ችግር ማስተናገድ ተችሏል።
በሀገራችን እና ህዝቦቿ ላይ በፀረ ሰላም ኃይሎች የተቃጡ የሽብር ወንጀሎችን ለመከላከል ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ አሁን ላይ ለተፈጠረው ሰላም የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ሀገርን ማጽናት ችሏል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሠራዊቱ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በሀገራችን የሚገኙ የአየር ማረፊያዎችን፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ስኳር ፋብሪካዎች፣ የማዕድን ማውጫዎችን በአማካኝ ከ600 በላይ ለሆኑ ታላላቅ መሠረተ ልማቶች እና ለሜጋ ፕሮጀክቶች ያልተቋረጠ የ24 ሰዓት ጥበቃ በማድረግ በፀረ-ሰላም ኃይሎች ሥራቸው እንዳይስተጓጓል ደህንነታቸውን ሙሉ በሙሉ ማስጠበቅ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ዕውቅና አግኝቶ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት በማደጉ ትምህርትና ስልጠና በአንድ ማዕከል እየመራ በለውጡ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ስድስት የማስተርስ እና ስድስት የዲግሪ ፕሮግራሞችን በመጨመር የዲግሪ መርሃ- ግብርን ወደ 16 ከፍ ያደረገ ሲሆን በጤና የትምህርት መስክም በደረጃ (Level) ይሰጥ የነበረዉን ወደ ሜዲካል ዶክትሬት ማሳደግ ችሏል።በቅርቡም የPHD ፕሮግራም የሚጀምር ይሆናል፡፡
የሠራዊቱን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ለረዥም ጊዜ ግንባታቸው ሲጓተት የነበሩ ፕሮጀክቶች የአርባምንጭ፣ የጅማ፣ የአሶሳ፣ የሰመራ፣ የድሬዳዋ፣ የጋምቤላ፣ የጅግጅጋ፣ የሀዋሳ እና የጎንደር የመኖሪያ ካምፖችና ቢሮዎች እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
በፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀግኖች ማዕከል በማስገንባት በግዳጅ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው አመራርና አባላት የሚያገግሙበትና ሥልጠና ወስደው ተስፋ ሰንቀው በቀጣይ ሕይወታቸውን ለመምራት በሚያስችላቸው መልኩ ሁለገብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲገነባ፣ ሪፎርሙ ፍሬ እንዲያፈራና ፖሊስ የመነሳት ዘመን ላይ እንዲደርስ ተገቢውን አመራር ለሰጣችሁ ስትራቴጅክ አመራሮች እና በተልዕኮ አፈፃፀም ለሀገር ክብር አለኝታ ሆናችሁ በተለያዩ ግዳጆች ላይ መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገር ላፀናችሁ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት አመራርና አባላት በኢትዮጵያ ፖሊስና በራሴ ስም ላቅያለ ክብርና ምስጋና አቀርባለሁ።
የኢትዮጵያ ፖሊስ የመነሳት ዘመንን ለማሳካት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት እንድንረባረብ ጥሪ እያቀረብኩ በድጋሜ እንኳን ለ116ኛው ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀን አደረሰን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ።
አመሰግናለሁ!
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ
የግሎባል ፐብሊክ ሴኩሪቲ ትብብር ቦርድ አባል