የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የሪፎርም ስኬቶች
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ አልፎ ለዘመናት ህዝብንና መንግስትን እያገለገለ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ሞዴል የሕግ አስከባሪ ተቋም መሆን የሚያስችለውን ሥር-ነቀል ሪፎርም በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ፖሊስነት የሀገርን ሰላምና ደኅንነት የሚያፀና ክቡር ሙያ ነው፡፡ አገልግሎቱ ከሚመጣውና ከሚሄደው የመንግስት ሥርዓት ጋር አብሮ እየፈረሰ ከዜሮ የሚጀምር ሳይሆን በየጊዜው እየዘመነ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር እና የሚዘልቅ ነው።
ተቋሙ ቀደም ሲል በፈፀማቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረውን ተዓማኒነት አጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሪፎርሙ አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመዘርጋትና በሥር-ነቀል ለውጥ ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጎ ልዩ ልዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ስኬታማ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያው ወቅቱን በሚመጥን ሁኔታ የአጠቃላይ ፖሊስ ሠራዊቱን 87% የሰው ኃይል እንዲይዝ ተደርጎ እንደ ገና በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል።
ጠቅላይ መምሪያው መረጃ መር እና ህብረተሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል መርህን (Intelligence Led and Community Policing Crime Prevention principles) በመከተል በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። በሥሩ የፈጥኖ ደራሽ፣ የፀጥታና ተቋማት ጥበቃ እንዲሁም የአስተዳደርና ድጋፍ አገልግሎት ዋና መምሪያዎችን ይዟል።
የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፡- ከዚህ ቀደም የነበረውን የተቋማት ጥበቃ ወሰን በማስፋት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስምሪት በመውሰድ በ10 መምሪያዎች (ክፍለ ጦሮች) እንዲደራጅ ተደርጎ በርካታ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም ፀረ-ሰላም ኃይሎችን እና አሸባሪዎችን የመመከት፣ የድንበር ቁጥጥር የማድረግና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን የመከላከል ብሎም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም በቀጥታ ለጠቅላይ መምሪያው ተጠሪ የሆነው የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ (Special Anti-Terrorism-SAT) ከፌደራል፣ ከክልል የፀጥታ አካላት እና ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ስኬታማ ኦፕሬሽን በማካሄድ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እያሰፈነ ይገኛል፡፡
የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አካል የሆነው SWAT ቡድን ልዩ ስልጠና ያለው እና በዘመናዊ ትጥቆች የተደራጀ እንዲሁም በየዓመቱ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚደረገው SWAT CHALLENGE ውድድር ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ሲሆን በየትኛውም ስፍራ የሚንቀሳቀስን የታጠቀ የሽብር ቡድንን ሴራ ማክሸፍ የሚችል ሆኖ የተደራጀ ውጤታማ የሥራ ክፍል ነው።
የፀጥታና ተቋማት ጥበቃ ዋና መምሪያ፡- ይህ ዋና መምሪያ የአድማ መከላከል፣ የአቪየሽን፣ የቪአይፒና ዲፕሎማቲክ፣ የዩኒቨርሲቲ፣ የተቋማት፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ፣ የማዕድንና ቱሪዝም ፖሊስ የተባሉ አዳዲስ መምሪያዎችን በማደራጀት ውጤታማ የወንጀል መከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የተቋማት ጥበቃ፡- የኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ፖሊስ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ከ898 በላይ የሚሆኑ የመንግስትና የግል መሰረተ ልማቶችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የነዳጅና ማዕድን ማውጫዎችን እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችን ጥበቃ ከመስጠት ባለፈ በየዓመቱ ከ500 በላይ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ እያደረገ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመውና በውሃ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የደህንነት ስጋቶችን በብቃት የሚጠብቀው የባሕር ላይ እና ዳርቻዎች ጥበቃ ፖሊስ (ኮስታል ጋርድ ፖሊስ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ላይ ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
የምድር ባቡር ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ፡- በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ላይ የሀገርን ወጪና ገቢ ንግድ ደህንነት ሲያስጠብቅ፣ የአቪዬሽን ፖሊስ ደግሞ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን ጨምሮ በሀገራችን የሚገኙ የአየር ማረፊያዎችን በመጠበቅ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ በረራዎችን ሰላማዊ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ፡- ይህ መምሪያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተመድቦ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርስቲዎች ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶችን በማስቀረት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆንና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናና ሌሎች ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስችሏል። በዚህም በሥነ-ምግባር የታነፀ በዕውቀት የበቃ ትውልድ እንዲፈጠር እና የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።
በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተረጋጋ የትምህርት አካባቢ በመፍጠር የተማሪዎችንና የመምህራንን ደኅንነት ከመጠበቁም ባሻገር በተቋማቱ ውስጥ የሚገኙ ውድ የላቦራቶሪና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም ምርምር የሚደረግባቸው ሀብቶች እንዳይወድሙና እንዳይዘረፉ በመከላከል ረገድ የማይተካ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው።
ይህ የሰላም እና የአስተማማኝ ደህንነት መረጋገጥ የወላጆችንና የማህበረሰቡን ስጋት ከመቅረፉም በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የብዝሃነት የአንድነትና የመቻቻል መድረክ ሆነው እንዲቀጥሉ ማስቻሉ የሪፎርሙ ትልቁ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል።
የአድማ መከላከል ፖሊስ፡- በዘመናዊ መልኩ የተደራጀው የአድማ ብተና ኃይል፣ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በዘመናዊ የፖሊስ ጥበብ የመቆጣጠር፣ ሰላማዊ ሰልፎችን እንዲሁም የተለያዩ ሁነቶችን የማጀብ፣ የመጠበቅና ሰላምን የማስከበር የዳበረ ልምድ ያለው እና ሕገ-ወጥነትን የመከላከል ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ የፖሊስ ኃይል ነው።
ቪ.አይ.ፒ (VIP)፡- የVIP ጥበቃ ፖሊስ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን እና የቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት በሚገባ እየጠበቀ፤ የዲፕሎማቲክ ጥበቃ ፖሊስ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የኤምባሲዎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሚናውን በልዩ ሁኔታ ተደራጅተው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በጀግንነት እየተወጡ ይገኛሉ።
የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ወንጀልን በብቃት ለመከላከል ህብረተሰቡ ተቋሙ ባበለፀጋቸው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) እና የስማርት ፖሊስ ጣቢያ (SPS) እንዲሁም የ991 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም በኮማንድ እና ኮንትሮል ማዕከል በኩል ወደ ተቋሙ የሚያደርሳቸውን ጥቆማዎች በመቀበል ውጤታማ የወንጀል መከላከል ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ጠቅላይ መምሪያው ደህንነቱ ከተጠበቀ ከፖሊስ ዲጂታል ሬዲዮ ግንኙነት፣ ከሲሲቲቪ፣ ከዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ EFPApp፣ ከ991 ነፃ የስልክ መስመር፣ ከድሮኖች ቅኝት እና ከሰው አልባ ስማርት የፖሊስ ጣቢያ በተቀናጀ ስርዓት (Integrated system) የተሰበሰበውን ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን በመጠቀም የወንጀል መከላከል ሥራውን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነ ነው።
ስፒር Special Program for Embassy Augmentation and Response (SPEAR)፡- ይህ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ለዲፕሎማቶቹ ደህንነት አጣዳፊና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል የላቀ ስልጠና የተሰጠው የድንገተኛ አደጋ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ኃይል (Quick Response Force) ነው። ፕሮግራሙ ኤምባሲው ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር ያለውን የመረጃ ልውውጥና የቴክኒክ ትብብር እንዲጠናከር አድርጓል።
ከአሜሪካ ኤምባሲ የደህንነት መስፈርቶች ጋር የሚጣጣም የጥበቃ ፕሮቶኮል በመዘርጋት ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ኤምባሲው መደበኛ የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎቹን ያለ ምንም ስጋት በሰላም እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የስፒር ፖሊስ አባላትም ያገኙትን ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮ ለሌሎች የፖሊስ አባላት ማካፈል እንዲችሉ ዕድል ተፈጥሯል።
በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በተቋማዊ አደረጃጀት ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣው የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ከሪፎርሙ በፊት የነበረውን ኋላቀር ትጥቅ እና ሎጀስቲክስ በቁጥርም በጥራትም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል። አሁን ላይ ያደጉ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የታጠቁ ዘመናዊ ብረት ለበስ (BRDM 2)፣ ዲጂታል አውቶማቲክ መሣሪያዎች፣ ፀረ-ፈንጅ፣ የውሃ መርጫና የሮድ ብሎከ መኪናን ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ባለቤት በመሆን የማድረግ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ K9 ክፍል፡- በወንጀል መከላከል እና በምርመራ ሥራዎች ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ይህ ክፍል ከእስራኤል ፖሊስ እና ከሌሎች ሀገራት ዓለም አቅፍ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት የተገኙ አነፍናፊ ውሾችን በመጠቀም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ ዋና ዋና የክልል ትራንዚት ኮሪደሮች እና ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ቦታዎች ላይ አቅሙን በእጅጉ አጠናክሮ ወንጀልን እየተከላከለ ይገኛል።
እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ውሻዎች የአደንዛዥ ዕፅ፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመለየት፣ ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል እና ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ምርቶችን በመቆጣጠር ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም ዓለም አቀፍ እና የተደራጁ ወንጀሎችን ከመከላከል አንፃር ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ነው።
የትራፊክ ፖሊስ፡- የመንገድ ትራፊክ አደጋን የመቀነስና አደጋዎችን የመመርመር ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ከተማ አምስቱም መውጫና መግቢያ በሮች እንዲሁም በክልል ከተሞች ዋና ዋና መንገዶች የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው አካባቢዎች ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ የትራፊክ ህግና ደንብን የተላለፉ 109,691 አሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡
የፈረሰኛ ፖሊስ ዋና ክፍል፡- የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርሙ ማዕቀፍ የፈረሰኛ ፖሊስን ለማቋቋም በዕቅድ ይዞ ሲተጋ ቆይቷል። ሦስት መቶ እግረኛ ፖሊሶች ሊሸፍኑት የሚችሉትን የወንጀል መከላከል ሥራ በአንድ ፈረሰኛ ፖሊስ ብቻ መሸፈን የሚያስችለውን የፈረሰኛ ፖሊስ ዲፓርትመንት አቋቁሞ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን አሁን ላይ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ኮንትሮባንድ ቁጥጥር፡- መምሪያው ህጋዊ ነጋዴዎችን የሚጎዳና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያቀጭጨውን ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከ2013-2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ብቻ 53,198,560,123 ብር የሚገመት የወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዝ ችሏል፡፡
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ከ2013-2017 ዓ.ም ድረስ በተደረገ ኦፕሬሽን ሊመዘበር የነበረ ብር 1,427,605,941፣ ዶላር 11,257,136፣ ዩሮ 170,300፣ ፓዉንድ 375,611 ሀብትን ከ747 ተጠርጣሪዎች ጋር ሕግ ፊት ማቅረብ ተችሏል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የነዳጅ ዕጥረት ተገን በማድረግ ነዳጅና ምርት በመደበቅ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ በማከማቸት ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትና ዕጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነትን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋልና ለሕግ በማቅረብ ለሀገር ኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ከ5,562 በላይ VIP እና ዲፕሎማቶች በተሳካ ሁኔታ የታጀቡ ሲሆን ከውጭ ሀገር የገቡ ከ65,021 በላይ ግዙፍ ማሽነሪዎችና ንብረቶችም ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ተታልለው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር የሚሰደዱ ዜጎችን ለመጠበቅ ሰፊ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም በየዓመቱ፣ በተለይም በአፋር፣ በአማራ (መተማ)፣ በኦሮሚያ (ሞያሌ) እና በሶማሌ (ሺንሌ እና ቶጎ ዉጫሌ) ባሉ የድንበር አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በሰላም ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እያደረገ ይገኛል።
የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት፡-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገር ውስጥ ከክልል፣ ከምስራቅ አፍሪካ፣ ከአህጉራዊ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የፖሊስ ተቋማት ጋር ያለውን የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት በማጠናከር የሎጀስቲክስ ድጋፎችን አግኝቷል፡፡ ለበርካታ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የውጭ ትምህርትና ስልጠና ዕድሎችን በማመቻቸት መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ተቋሙ በማምጣት ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከል አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል በሪፎርሙ በተሰራው ስኬታማ ተግባር በጀግንነት የዜጎችን ሕይወት እየታደገ፣ ሰብዓዊነትን ተላብሶ ሕዝብን እያገለገለ የሀገርን ሰላምና ደህንነት እያፀና ያለ የፖሊስ ኃይል ሆኗል።
ጠቅላይ መምሪያው በተቋማዊ ሪፎርም የተጀመረውን የልህቀት ጉዞ በማስቀጠል ተቋሙ በ2022 በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፖሊስ ተቋማት ውስጥ የሚመደብ፤ ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ፤ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ተፈጥሮ ለማየት ሰንቆ የተነሳውን ራዕይ ለማሳካት በላቀ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
የታተመበት ቀን:-2026-08-31