የኮሚሽነር ጄኔራል መልዕክት

photo_2022-03-30_17-55-54 (2)_1650961997.jpg

በ2014 ዓ.ም ሀገራችንን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጪ ተቀናጅተው የተነሱብንን ጠላቶቻችንን በተባበረ ክንድ በመመከት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ታላቅነት የታየበት እንዲሁም በውስጥ የተደራጁ የሽብር ኃይሎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ውድመት ሲያስከትሉ የነበሩት ላይም ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ጠንካራ እርምጃ የተወሰደበትና እየተወሰደ ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም ብቃት ያለው የሰው ኃይል በጠንካራ አደረጃጀትና ትጥቅ በማዘመን የተሰጠውን ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት በፍፁም ጀግንነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

በዚህም ተቋሙ ወንጀልን በብቃት ከመከላከል አኳያ በአዲስ መልክ ጠንካራ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ኃይል በማደራጀት የሰው ሃይሉን በከፍተኛ ቁጥር አሳድጎና ብቃቱን በስልጠና አጎልብቶ፤ ዘመናዊ ትጥቆችን በማስታጠቅ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በመላ ሀገሪቱ ስምሪት ወስዶ የሕይወት መስዋትነት እየከፈለ የሀገርን ደህንነትና የዜጎችን ሰላም በማስጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባ አከናውኗል።

እንዲሁም የወንጀል ምርመራ ሥራችን ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት በሙስናና በታክስ ስወራ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሀገር ሀብት ከምዝበራ ማዳን ተችሏል፡፡

በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተፈፀሙ የተደራጁ የወንጀል እና የሽብር ድርጊቶችን በማጣራት አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ የተሰራ ሲሆን በፎረንሲክ የምርመራ ዘርፍ DNAና ሌሎች ዘመናዊ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል።

በሌላ በኩል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የኮማንድ ኮንትሮል ማዕከልና የዲጅታል ግንኙነት ራዲዮ ባለቤት በመሆን የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራችንን በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተፈጥሮል፡፡

ውድ ኢትዮጵያዊያን እና መላው የሀገራችን ፖሊሶች የሁላችንም አሻራ ያረፈበትን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በፀረ-ሰላም ኃይሎች እንዳይደናቀፉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር 24 ሰዓት በጀግንነት በመጠበቅ ለውጤት እንዲበቁ አድርጓል፡፡ እየጠበቀም ይገኛል፡፡

በመጪው አመትም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራባቸው ካቀድናቸው ዋና ዋናዎች ውስጥም፡- የውጭና የውስጥ ኃይሎች በሽብር ተግባር ተሰማርተው በህዝባችን ላይ የሚያደርስቱን ሞትና መፈናቀል ለማስቀረት ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተንና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በተደራጀ መንገድ በሀገር ሀብትና ንብረት ላይ ዘረፋ የሚፈፅሙ ሙሰኞች ላይም የተቀናጀ ኦፕሬሽን በማካሄድ ህግ ፊት የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

አሸባሪው የህውሃት ቡድን ከመንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተብንን ጦርነት መላው የሀገራችን የፖሊስ ኃይል ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና ከጥምር ኃይሉ እንዲሁም ሰላም ወዳዱ ህዝባችን ጎን በመሰለፍ በተባበረ ክንድ በመመከት ኃላፊነታችንን በታላቅ ጀግንነት በመወጣት፣ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ድርሻ የምንወጣ ሲሆን በአጠቃላይ የወንጀል መከላከልና የምርመራ አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በትጥቅ፣ በቴክኖሎጂ እና በሎጀስቲክስ ይበልጥ ተጠናክረንና ልዩ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት ዓመት ይሆናል፡፡

የአዲሱን ዓመት በዓልን እና በቀጣይ የሚከበሩትን ሀይማኖታዊ፣ ህዝባዊ እና መንግስታዊ ሁነቶችን ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ችግር ህብረተሰቡ በድምቀት እንዲያከብር የሀገራችን የፖሊስ ኃይል በማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጣለሁ፡፡

በመጨረሻም መላው የሀገራችን ህዝብና የፖሊስ ኃይል ከምንጊዜውም በላይ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጥሪዬን እያቀረብኩ በድጋሚ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የብልፅግና እና የአንድነት ይሆንልን ዘንድ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡

 

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

©2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ