የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማኔጅመንት አባላት በመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ተገኝተው የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢፌፖሚ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማኔጅመንት አባላት እና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ማዕከልን ጎብኝተው የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

450434262_861289346029450_7522116841335959272_n_1720707059.png

ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጉብኝት አድርገው የገንዘብ ድጋፉን ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ማዕከል ባስረከቡበት ወቅት “ሰው ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የሚለውን መሪ ቃል መሠረት አድርጎ በመነሳት ሀገራችንን በተለያዩ ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ ጠዋሪ ያጡ አባቶች እና እናቶች የበጎ ሥራዎች ማሳያ በሆነው ማዕከል ከነ ማኔጅመንታቸው እና ከሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ለእነዚህ በጎ ሥራ ምክንያት የሆኑትን ዶክተር ቢኒያም በቀለን አመስግነዋል።

ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ውለታን የማይረሳ በህወይት መስዋዕትነት ሀገር የሚጠብቅ በመሆኑ በየዓመቱ ሐምሌ አራትን በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ቀኑን አብረን የምናከብርበት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማዕከሉን እንደ አንድ አካል በመቁጠር ዘላቂ በሆነ መንገድ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በጎነት ሁሌም መባረክ ነው ብለው የሀገር ትልቅ ውለታ ባለቤት የሆኑ አባቶችን እና እናቶችን እንደ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማገዝ ስለአለብን ተቋማችን የሚችለውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ማዕከል መሥራች ዶክተር ቢኒያም በቀለ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የማኔጅመንት አባላት እና ከፍተኛ አመራሮችን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ለተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ በመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ማዕከል ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

የታተመበት ቀን:-2024-07-11
ተጨማሪ ዜናዎች